“በውሸት በሄዱበት መንገድ መመለስ ያስቸግራል”
"በውሸት በሄዱበት መንገድ መመለስ ያስቸግራል"
ከሰላም ለአንድነትና ለሕግ የበላይነት የተቋቋመ መድረክ የተሰጠ መግለጫ።
በካህኑ ተመርጠው ከተሾሙት የዊኒፔግ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቦርድ አባላት አንዱ በመድረክ አባላት ላይ በቅርቡ ሀሰተኛ የሆነ የማደናገሪያ ወሬ እያሰራጨ መሆኑን ደርሰንበታል። ይኸውም "የመድረክ አባላት በቤተ ክርስቲያኑ ላይ አቅርበውት የነበረውን ጥያቄ አንስተዋል። እኛም [የቤተ ክርስቲያንዋ አስተዳደር] በጉዳዩ ተስማምተናል" የሚል ነው።
እነዚህ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ከማቋቋምና እስከ መጨረሻው ድረስ ከቤተ ክርስቲያኑ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደነበረ እየታወቀ በካህኑ ከቤተ ክርስቲያናቸው መታገዳቸው ሳያንስ፤ ይህን የመሰለ ተራ የሐሰት ዜና ማሰራጨቱ ምን ለማትረፍ ተፈልጎ እንደሆነ ከቶ ሊገባን አልቻለም። ይኸውም "በውሸት በሄዱበት መንገድ መመለስ ያስቸግራል" የሚለውን ብሂል ያስታውሰናል። ያሁኑ ነጭ ውሸት ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ በየቤቱ እየደወሉ እርዱኝ
ከተባለው ዘመቻ የተለየ ሆኖ አላገኘነውም። ይህ ሙከራ እየዋለ ሲያድር እውነትን ለመሸፈን ፍትህን ለማጓደል የተደረገ የሃሰት ዘመቻ መሆኑን ጠቅላላው ምዕመን የተረዳውና ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው።
መድረክ ከተመሠረተበት አጭር ጊዜ ጀምሮ አባላቱ በጋራ በመሆን ይህንን ሕገ ወጥ አሠራር እርቃኑን ለማስቀረት በመረጃ የተደገፉ እውነታዎችን ለቤተ ክርስቲያኑ ምዕመናንና ለአንባቢ ሁሉ ግልጽ ለማድረግ ችለዋል። በዚህ አካሄድ ነው መድረክ ሥራውን ሲያከናውን የቆየው። መድረክ የተቋቋመው ማንንም ለመጉዳት ወይም የማንንም ዝና ጥላሸት ለመቀባት ሳይሆን፤ ሰላም አንድነትና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ምዕመናንም በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ እምነት አድሮባቸው በእኩልነት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ ነው። የመድረክ አባላት አንድነታቸውን በማጠናከር ተቀባይነት ባለው በጋራ መማማርን እርስ በርስ መከባበርና መተማመንን በማጐልበት በዚሁ ልምድ ምዕመናኑን ሁሉ ለማሳተፍ ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል። መድረክ ይህንኑ አላማውን ለማስፈጸም እንቅፋቱን ሁሉ በመቋቋም በጽናት ቆሟል።
መድረክ ተቃራኒ ሃሳቦችን ከማግለል ይልቅ በአግባቡ በማስተናገድ አባላቱ ጠንካራ በሆነ የጋራ መሠረት ላይ እንዲቆሙ ይጥራል። የመድረክ አባላት ከየግል ልምዳቸው በመማማር ይህንኑ ልምድ በምዕመናኑ መካከል በማስረጽ በመተማመንና በመከባበር የተመሠረተ ጤናማ ግንኙነትን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማስፈን ይሠራሉ። መድረክ የያንዳንዱን አባል ተሰጥዎና እውቀት በልምድ ልውውጥ በማዳበር የመተሳሰብንና የመደጋገፍን ባህል በመሃከላቸው እንዲሰፍን ያበረታታል። ግባቸውም ከግል ጥቅም ይልቅ ወደ ጋራ ጥቅምና እድገት እንዲያተኩር ይረዳል። የመድረክ አባላት ከወሬኞችና ከሀሜተኞች የሚለያቸው ዋናው ነገር ለቆሙለት
ዓላማ ግብ መምታት በቁርጠኝነት ጠንክረው በመሥራታቸው ነው። መድረክ በቁርጠኛነትና በትጋት የተጋፈጠው ተግባር በረጅም ጊዜ ሂደት ሰላም ሕብረትና ሕጋዊ አሠራርን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንደሚያሰፍን እርግጠኞች ነን። የኛ ቃል ኪዳን የግልና የሕብረተሰቡን ጥንካሬ መሠረት በማድረግ ለጋራ ደህንነትና እድገት ማትጋት ነው።
መድረክ በየጊዜው የደረሰበትን ደረጃ በዚህ ድረ ገጻችን የምንገልጽ ስለሆነ ከዚህ ውጭ በሃሰተኞች የሚወራው ሁሉ ተጨባጭነት የሌለው ተራ አሉባልታ መሆኑን እናስታውቃለን። ስለዚህ በሃሳብ ከኛ ጋር ለቆሙትም ሆነ ከኛ የተለየ ሃሳብ ለሚያራምዱት ግልጽ እንዲሆን የምንፈልገው የረጅም ጊዜ ግባችን
በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሕግና ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ መሆኑን ልናረጋግጥ እንወዳለን።
እግዚአብሔር ወደ ሰላምና ፍቅር እንዲመራን ፈቃዱ ይሁን።