ደመራ - ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
እንኳን ለ፳፻፯ ዓ.ም. የደመራ በዓል አደረሳችሁ?
ከሶስት ዓመታት በፊት ስለ ደመራ ታሪክ በዓል ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ (በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባሕላችን
አንጻር) ጽፈው አቅርበውልን ነበር። ከዚያ በፊት ቅድስት እሌኒ ጌታችን ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነበትን መስቀል ከተቀበረበት
ቦታ ማውጣቷን እና ግማደ መስቀሉም ወደ ሀገራችን ገብቶ ግሸን መቀመጡን ነበር። ይሁን እንጂ አባቶቻችን
በእምነታቸው አንጻር ከሚሰጡት ክብር ባሻገር፤ ደመራ የሚል ስያሜ በመስጠት በልማዳዊ አከባበርም ሳይወሰኑ፤
ከራሳቸው ባህልና ስሜት ጋራ ደምረውና አዋህደው በዘመናቸው ለገጠማቸው ችግር መፍቻ አርገው እንደተጠቀሙበት
በተብራራ ሁኔታ አልቀረበልንም ነበር።
ንግስት እሌኒ ኢትዮጵያዊት አለነበረችም። እሌኒ መስቀል ከደመራ ጋራ አላቃጠለችም። ተግባሩንም በኢትዮጵያ
ምድር አላደረግችውም። ደመራ ብላም አልሰየመችውም። እሌኒ በዘመኑ የገጠማት ችግር ግማደ መስቀሉ ተቀብሮ መደበቁ
ሲሆን፣ የእሌኒ ምኞትና የፈጸመችው ተግባር መስቀሉን ከተቀበረበት ፈንቅሎ ማውጣት እንደነበረ ጽሑፉ ያብራራል ።
ጽሑፉ በዝርዝር እንዳቀረበው ፤ በየዘመኑ ለደመራችን፣ ለአንድነታችን ተቃራኒ በመሆን የሚከሰቱ ጠላቶች
እንዳሉ ይገልጽና፤ ዛሬም ሐገራችን ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ መውደቋን ያሳያል። ቤተ ክርስቲያናችንም በዚያ
ዘመን ከፖርቱጋል በመጡ ሮማውያን መነኮሳት ወንደ ላጤዎች ተወራ እንደነበር፤ ዛሬም ከኢትዮጵያውያን አብራክ በወጡ
ቆሞሳት (ወንደ ላጤዎች) ተወራለች።
ታዲያ በዚህ ዓመት ከደመራችን የሚነሳው እሳት ሙቀት የሚሰጥ፤ብርሃን የሚያመነጭ፤ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ
እምነታችንን የሚያብለጨለጭ፤ ብሄራዊ ስሜታችንን የሚያግልና የሚያጋግል፤ ገለባውን የሚበላ፤ ጭራሮውን አመድ፤
ግንዱን ከሰል የሚያደርግ መሆን አለበት። ግልብ የሆነውን ስሜታችን ማ ለማስገንፈል በሽብሸባው፣ በመዝሙሩ ላይ
ህሊናችንን ማንጠልጠል የለብንም። ለችግራችን መፍትሄ ማፍለቅ የምንችለው፤ ያለፉትን አባቶች፤ ከራሳችን ጋራ፤ ዘመኑን
ከዘመን፤ ችግሩን ከችግር፤ ምክንያቱን ከምክንያት፤ ጥቅሙን ከጥቅም ጋራ ማስተያየት ስንችል ብቻ ነው። ለገጠመን ችግር
መፍቻ፤ ለጠፋብንም መፍትሄ ማግኛ ፣ የተሰወረውንም እንድናይ ዓይነ ልቡናችንን የተሰቀለው ክርስቶስ ያብራልን! ስለ
ደመራው በዓል በጥልቀት ያስተምራል ብለን ስላሰብን በዚህች አጭር ማሰሰቢያ አባሪነት ጦማሩን እንደገና አቅርበነዋል።